❶
ነሃሴ 1 1966። አንድ የ25 አመት ወጣት ትልቅ ህንጻ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድንገት መተኮስ ጀመረ። በዚህ ትራጄዲ 13 ሰዊች ሲሞቱ፣ 33 ቆሰሉ። ፖሊስም በመጨረሻ ወጣቱን ተኩሶ ገደለው። ፖሊስ ወጣቱ ቤት ሲሄድ ሁለት አስክሬን አገኘ—የእናቱንና የሚስቱን። ይህ ወጣት ሁለቱንም የገደላቸው፣ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነበር።
በጣም አስገራሚው ነገር፣ ፖሊስ የወጣቱ ቤት ውስጥ ይህንን ትራጄዲ ለመፈጸም የሚያነሳሳው ምንም ምልክት አላገኘም። ወጣቱ የስካውት አባል፣ የባንክ ሰራተኛና የምህንድስና ተማሪ ነበር።
ወጣቱ አናቱንና ሚስቱን ከገደለ በኋላ ኑዛዜ መሰል ነገር ጽፎ ተገኝቷል። ኑዛዜው እንዲህ ይላል።
"ከቅርብ ግዜ ወዲህ ራሴን ለመረዳት አልቻልኩም። ኃላፊነት የሚሰማው፣ ብልህ ወጣት ነበርኩኝ። ነገር ግን ከግዜ ወዲህ(እርግጠኛ ቀኑን አላስታውሰውም) እንግዳ የሆኑ መሰረተ-ቢስ ሃሳቦች በአእምሮዬ ይመላለሱብኛል። ከሞትኩ በኋላ ምርመራ ተደርጎብኝ፣ ያለብኝ አካላዊ ግድፈት እንደሚጣራ ተስፋ አደርጋለሁ።"
ወጣቱ የጠየቀው ተፈቅዶ የሬሳ ምርመራ ተደረገለት። ታዲያ ዶክተሮች አንድ አስገራሚ ነገር አገኙ። በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ትንሽ እጢ ተገኘ። እጢው አሚግዳላ የሚባለው የአእምሮ ክፍሉን ተጭኖት ተገኘ። አሚግዳላ ደግሞ በአእምሯችን ፍርሃትን የሚቆጣጠር አካል ነው። ወጣቱ ከመጠን በላይ የሆነ ፍርሃት ተሰምቶት ነው ያንን ሁሉ ትራጂክ ግድያ የፈጸመው። አለበለዚያ በወጣቱ ባህሪ ውስጥ እነዲህ ያለ ተግባር ሊፈጽም ይችላል የሚያስብል አንድም አጣራጣሪ ነገር አልነበረም።
❷
ሄንሪ የሚጥል በሽታ የጀመረው ገና በ15 አመቱ ነበር። ከዚያ ወዲህ ህመሙ ይበልጥ እየከፋ መጣ። በመጨረሻ ሄንሪ ገና በሙከራ ላይ ያለ የአእምሮ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ተስማማ።
ህክምናው ተደረገ። ከሄንሪ አእምሮ ሁለቱም ክፍሎች ሂፖካምፐስ የተሰኘ ክፍሉን በከፊል አስወገዱት። የቀዶ ህክምናው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ሄንሪ ከሚጥል በሽታው ዳነ።
ነገር ግን ዶክተሮቹ ያላሰቡት ነገር ተፈጠረ። ሄንሪ ምንም አይነት አዲስ የማስታወስ ተግባር መፈጸም አልቻለም። ይህ ብቻ አይደለም። ሄንሪ የወደፊቱን ግዜም በምናብ መሳል አይችልም። የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ሂፖካምፐስ የሚባለው፣ በአእምሯችን ውስጥ የሚገኝ አስታዋሽ ክፍል ከሄንሪ አእምሮ በመወገዱ ነው።
❸
ማይከ የማየት ችሎታውን ያጣው ገና በሶስት አመቱ ነበር። የኬሚካል ፍንዳታ ተፈናጥሮበት አይነስውር ሆነ። አይነስውር ሆኖ የተሳካለት የቢዝነስ ሰው፣ ከዚህ በተጨማሪ በፓራሎምፒክ የበረዶ ሸርተቴ ውድድር ሻምፒዮና ሆነ።
ከ40 አመት በኋላ ዶክተሮች ዳግም የማየት ተስፋ እንዳለው ነገሩት።። እሱም ቀዶ ህክምና ለማድረግ ተስማማ። ቀዶ ህክምናው በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ። ከህክምና ሳይንስ አንጻር ውጤታማ ነበር፤ ከማይክ አንጻር ግን ጉዳዩ ሌላ ነው።
አያችሁ! ከቀዶ ህክምናው በኋላ የማይክን አይን የሸፈኑ ሻሾች ሲፈቱ አይኑ የሚያጥበረብር ብርሃን ገጠመው። ማይክ ግራ ተጋባ። ማየት ቢችልም፣ ማየት አይችልም ነበር።
የተፈጠረውን ጉዳይ አብረን እንይ። እንግዲህ አይን እንደ ካሜራ አይደለም። ለማየት አይን ብቻውን በቂ አይደለም። ያየነውን ነገር ፕሮሰስ አድርጎ የሚረዳ አእምሮ ያስፈልጋል። ማይክ በሶስት አመቱ ሲታወር፣ አእምሮው ውስጥ ምስልን ፕሮሰስ የሚያደርግ አካል፣ የድምጽና ሌሎች የስሜት ህዋሳቶችን ፕሮሰስ ወደማድረግ ተሻገረ። ከዚህ የምንረዳው የአእምሮን ዳይናሚክ ባህሪ ወይም ተለዋዋጭነት ነው። አእምሮ ረግቶ ፓሲቭ ሆኖ አይቀመጥም። ራሱን ከተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ያዛምዳል። ለማየት አእምሮ ውስጥ በቢሊየን የሚቆጠሩ ኒውሮኖች ይሳተፋሉ። በማይክ ኬዝ እነዚህ ኒውሮኖች ለ40 አመታት ስራ ሳይፈቱ የማይክን ሌሎች ስሜቶች(መስማት፣ መዳሰስ) ሲያግዙ ኖረዋል።
❹
አንድ ቀን ከሳንፍራንሲስኮ ተነስቶ በጀልባ ወደ ዝነኛው ደሴት አልካትራዝ አመራ። አልካትራዝ ላይ በውሃ የተከበበ እስርቤት አለ። የሚሄደው ጉድጓድ ውስጥ ያለ እስረኛ ለመጎብኘት ነው። አንድ ሰው በአለም ወንጀል ሲሰራ ወደ አልካትራዝ ይላካል፤ አልካትራዝ ውስጥ ደግሞ ወንጀል ሲሰራ ወደ ጉድጓድ ይላካል።
ጉድጓዱ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ነው። ምንም ነገር መስማት አይቻልም፤ ምንም ነገር ማየት አይቻልም። ነገር ግን ጉድጓዱ ውስጥ የታሰሩ ሰዎች የገጠማቸውን ሲናገሩ ስለ አእምሮ አስደናቂ ጠባይ ተገኘ። እንግዲህ እስረኞቹ በዚህ ጉድጓድ ውስጥ አይናቸውም ከማየት፣ ጆሮዋቸውም ከመስማት ቦዘነ። አእምሯቸው ግን ከውጪ ሌላ አለም እንዳለ አልረሳም። እና በዚህ አይንን ቢወጉ በማይታይበት ጨለማ፣ እስረኞቹ አእምሯቸው የፈጠረውን ምስል ማየት ቻሉ። ታዲያ ያዩት ህልም አይደለም። በእውናቸው ነው። ኒውሮሳይንስም ይደግፋቸዋል።
ኒውሮሳይንስ ምንድነው የሚለው? አእምሮ የምናየውን ነገር ምስል የሚፈጥረው ገና ነገሩን ሳናየው ነው። እስረኞቹ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለቀናት ሲያሳልፉ ምስል ማየት የቻሉት በዚህ የአእምሮ ጠባይ የተነሳ ነው። እስረኞቹ ምንም ነገር ባያዩም እንኳን፣ አእምሯቸው የራሱን ስራ ሰርቶ በግምት የሚያቀብላቸው ምስል አለ። ከአለም ብትነጠልም፣ ትእይንቱ ይቀጥላል። ደግሞም ጉድጓድ ውስጥ ሳንታሰር ሁላችንም ይህንን ልምምድ ዘወትር ማታ እንለማመደዋለን። እንቅልፋችንን ተኝተን ብዙ ነገር ስንሰማ፣ ብዙ ነገር ስናይ እናድራለን—ይህንንም አጋጣሚ ህልም ብለን እንጠራዋለን። ደግሞም በህልም የምናየውን በምናይበት ሰአት፣ እውነትነቱን ምንም አንጠራጠርም። ከነቃን በኋላ ነው ህልም መሆኑን የምናውቀው። በወቅቱ አይናችንም እያየ፣ ጆሯችንም እየሰማ አይደለም። አእምሯችን ግን በራሱ ሞዴል የምናየውን፣ የምንሰማውን እየፈጠረልን ነበር። የአእምሮ ነገር እጅግ አስደናቂ ነው።
❺
ከቀደመው ነጥብ እንደምንረዳው የምናየው በአይናችን አይደለም። በአእምሯችን ነው። የአይናችን ተግባር አእምሯችንን መርዳት ነው። እንዴት ነው የሚረዳው? አይን ከአካባቢው የምስል መረጃ የሚሰበሰብ አካል ነው። ነገር ግን የምናየው ይህንን የተሰበሰበ መረጃ አይደለም። አይናችን ምንም አይነት መረጃ ከመሰብሱ በፊት አእምሯችን የምናየውን መገመት ይጀምራል። የሚገምተው ከልምዳችን፣ ከሜሞሪ ወዘተ ተነስቶ ነው። አእምሯችን የገመተውን በአይን ከተቀበለው ጋር ያወዳድርና ስህተቱን አስቀርቶ ለቪዥዋል ኮርቴክስ ይልክለትና እናያለን።
ታዲያ የምናየውን ነገር ሁሉ አናይም። ይህንን እውነት ከኒውሮሳይንቲስቶች በፊት አስማተኞኝ ያውቁታል። በዚህ እውቀት ነው በእይታዎቻችን መካከል ባለ ቅጽበት፣ አስማተኞች አስማታቸውን የሚሰሩት—እያየን የማናየው ስላለ።
ግን አንድ ጉዳይ አለ። አእምሯችን ለምንድነው ሁሉንም የማያየው? ለምን ስህተት ይሰራል? አያችሁ! ሰውነታችን ከሚጠቀመው ኢነርጂ 20%ቱን የሚጠቀመው አእምሮ ነው። ታዲያ ይሄን ኢነርጂ በብቃት ለመጠቀም መቆጠብ አለበት። ስለዚህ ለቁጠባ ሲባል፣ አእምሮ እያጠጋጋ ይገምታል እንጂ፣ ፍጹም ልክ የሆነ ምስል አያሳየንም። ለምሳሌ ብዙ የመኪና አደጋዎች የሚደርሰት ሾፌሩ በአይኑ እያየ፣ በአእምሮው ሳያይ ሲቀር ነው።
❻
ቀለም መሰረታዊ የአለም ተፈጥሮ ይመስለናል። የሚገኘው ግን በአእምሯችን ብቻ ነው። አለም ቀለም አልባ ናት።
ሌላው ጉዳይ አይናችን ማየት የሚችለው ውሱን ዌቭሌንግዝ ነው—ከአጠቃላይ የዌቭሌንግዝ ውሰጥ 1/10,000,000,000,000 ብቻ። ስለዚህ በዙሪያችን ያሉ ብዙ የማናያቸው ነገሮች አሉ፦ ለምሳሌ ጋማ ዌቭ፣ ሬዲዮ ዌቭ፣ ማይክሮ ዌቭ፣ ኤክስ ሬይ ወዘተ።