ቢያረፍድም
(ከቡና ቁርስ መጽሐፌ ላይ)
----
ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው በቅርብ የሥራ ባልደረባዬ ግፊት ነበር፡፡
“በፊት የምሠራበት ቢሮ ነው የማውቀው” ብላ ጀምራ፣ ስለ መልካምነቱ ማዛጋት እስከጀምር ድረስ የሚያሰለቸኝ ዝርዝር ውስጥ ገብታ ታወራኝ ነበር፡፡
“በጣም ነው የምትግባቡት፤ በጣም፡፡ ሁለታችሁንም አሣምሬ ስለማውቃችሁ እርግጠኛ ነኝ ትግባባላችሁ” እያለች፡፡
እንድንገናኝ ያላት ጉጉት፣ ግኑኙነታችን እንደሚሠምር ያላት እርግጠኝነት አስገራሚ ነበር፡፡ አብራኝ ስለምትሠራና ስለምትውል፣ ውስጤን አብጠርጥራ የምታውቅ ይመስል፤ አብራው ትሠራ ስለነበር፣ እውነተኛ ማንነቱን አጥርታ ታውቅ ይመስል፣ “አሣምሬ ስለማውቃችሁ” ስትል ይገርመኛል፡፡ በዚያ ሰዐት፣ አዲስ ሰው ለመተዋወቅና አዲስ ፍቅር ለመጀመር ያለኝ ፍላጎት ሞቶ ነበር፡፡
ግን፣
“መቼ ነው ተስፋን የምታገኚው…? መቼ ልበለው…? ዛሬ ይመችሻል…? ዓርብ ይሁን?” እያለች መቆሚያ መቀመጫ ስታሳጣኝ፣ “እሺ” አልኳት፡፡
በዚያ ላይ፣ ከዚህ በፊት እንኳን በዐይነ ሥጋ፣ በፎቶ እንኳን ዐይቼው የማላውቀው ሰው ጋር፣ እራት ለመብላት ስስማማ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ ግን አንዳንዴ አዲስ ነገር መሞከር አይከፋም፣ አይደል?
----
አርፍዶ ነበር፡፡ ሃያ አምስት ደቂቃ፡፡ ዝርክርክ፡፡ ዝርክርክ ወንድ አልወድም፡፡
አርፋጅ፣ ጥፍሩን የማይከረክም፣ ንጹሕ ያልሆነና ሲበላ ሥነ ሥርዓት የሌለው ወንድም አልወድም፡፡
በጣም ነው የሚቀፈኝ እንዲህ ዓይነቱ ወንድ፡፡ ያን ያህልም የጠበቅኩት፣ ለአፍታ ላቆመው ያልቻልኩት የሕይወት ተፈራ ቅመም የሆነ መጽሐፍ “ማማ በሰማይ” መስጦ ይዞኝ ነው፡፡
ሲደርስ፣ ይቅርታውን አዥጎደጎደው፡፡
አለባበሱ ጥሩ፣ ንጹሕና ለዐይን የሚጥም ዓይነት ሰው ሆኖ አገኘሁት፡፡
“ሌላኛው በእምነት ሬስቶራንት ተሳስቼ ሄጄ” ነው አለኝ፡፡ ሌላ በእምነት ሬስቶራንት እንዳለ አላውቅም ነበር ግን ይሁን፡፡
ያዘዝነውን በየዓይነቱ በጥንቃቄና ሳይዝረከረክ በላ፡፡
ወሬ አላበዛም፡፡ እኔ ግን እንዳወራ አበረታታኝ፡፡
እኔ ብቻ ካላወራሁ አለማለቱን፣ ለረጅም ጊዜ ከወንዶች ያላገኘሁት እፎይታ የሚሰጥ ጠባይ ሆኖ አገኘሁት፡፡
ጥሩ ጊዜ አሳለፍን፣ አርፍዶ ከመምጣቱ በቀር፡፡
“አርፍዶም ቢሆን፣ እንኳን መጣ” አልኩ በሆዴ፡፡
ሕይወት ተፈራ፣ በመጽሐፏ መጣም፣ ለጥቂት ሊዘጋበት የነበረውን ቶሎ ቶሎ የማይከፈት የመልካም ዕድል በር ተከፍቶ እንዲቆይ ያደረገችለት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ታላቅ ውለታዋ እቅፍ አበባ ሊልክላት ወይ ደግሞ ጣባ ሙሉ ክትፎ ሊጋብዛት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እስካፍንጫው የታጠቀን የደርግ መንግሥት፣ “ አፍንጫህን ላስ” ላለች ቆፍጣናና እሳት የላሰች የስልሳዎቹ አራዳ፣ የትኛው እንደሚመጥናት እንጃ እንጂ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ስንገናኝ፣ ማኪያቶ ከጠጣን በኋላ እንደ አዲስ በሰፋውና በኤልኢዲ መብራቶች በተጥልቀለቀው የቦሌ ጎዳና ላይ በእግራችን ብዙ ሄድን፡፡
ያኔም ወሬው ሁሉ ከእኔ እንዲመጣ ፈቅዶ ስለራሱ ጥቂት ነገሮች ብቻ ነገረኝ፡፡ ዛሬ ግን ከዚህ በላይ እንዲያወራና ስለማንነቱ እንዲነግረኝ ፈልጌ ነበር፡፡ ወሬን እየጠረቅሁ፣ በመንገዳችን መሀል ቀድሜ ያላየሁት በውሃ የተሞላ ጭቃ ውስጥ በሁለቱም እግሬ ዘው ብዬ ስገባ ግን፣ ሌላ ነገር አስተዋልኩ፡፡ የበሰበሱ የስኒከር ጫማዎቼን ጎንበስ ብሎ ካየ በኋላ፣ ባሸበረከበት፣
“ አውልቂያቸውና ላድርቅልሽ” ሲለኝ ተረገምኩ፡፡
ይሄ ሰውዬ ምስኪን ነው ልጄ፡፡ ምስኪን፡፡
ለዐሥራ አንደኛ ጊዜ ተገናኝተን ቤቱ ስሄድ፣ አቧራ የወረሰውን የሚያምር የዕንጨት የመጽሐፍ መደርደሪያውንና ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን አቧራ የጠጣ ጊታር ጊዜ ወስጄ አጸዳሁለት፡፡
ተመላላሽ ሠራተኛ ነበረችው፣ ግን ላይ ላዩን እንጂ በደንብ አታጸዳ ኖሯል፡፡ ያንን ማድረጌን እንደ ትልቅ ውለታ ወስዶ ፊቱ በፈገግታ በራ፡፡
ከዚያ፣ አሪፍ በቅመም ያበደ ሻይ አፈላልኝ፡፡
ግን ለመክሰስ ካልሠራሁ ብሎ የጠበሰው እንቁላል ፍርፍር፣ ድብን ብሎ አርሮ ነበር፡፡ ያም ሆኖ መሞከሩ አጣፈጠውና ጥርግ አድርጌ በላሁ፡፡
የዚያን ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሮቼን ቀመሳቸው፡፡
ከመጠን በላይ ጫን ብሎ አልሳመኝም፤ ለሌላ ነገር ቸኩሎ አላስጨነቀኝም፡፡ ሳም ብቻ አደረገኝ፡፡
ይሄ ጨዋነቱና እርጋታው ከበላሁት በፍቅር የተሠራ መክሰስና ከጠጣሁት አሪፍ ሻይ በላይ ጣመኝ፡፡
ለዐሥራ አራተኛ ጊዜ ስንገናኝ፣ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ መኝታ ክፍሉ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ያየሁትን ጊታር አወረደና ሙዚቃ ተጫወተልኝ፡፡ ለካስ ከዚህ በፊት ተጫወትልኝ ስለው፣ “ብዙ ጎበዝ አይደለሁም” ያለኝ ትህትና ይዞት ነው፡፡
የቴዎድሮስ ታደሰን “ እየቆረቆረኝ “ ዘፈነልኝ፡፡ ጊታር አጨዋወቱ ከጠበቅኩት በላይ ድንቅ፣ የእሱ ድምፅ ግን ያን ያህል አልነበረም፡፡
ቢሆንም አብሬው አደርኩ፡፡ ያንን ምሽት፣ በትህትናውና በቴዎድሮስ ዜማ ጭኖቼን ያስከፈተኝ የመጀመሪያው ሰው ሆነ፡፡
-----
ፍቅር ከጀመርን ከጥቂት ወራት በኋላ አንዱን ከሰዐት ከቤቴ መጣ፡፡
መንገድ ላይ ውሎ ሞቆት ስለነበር ቀዝቃዛ ሻወር ሊወስድ ገባ፡፡
ጨርሶ ሲወጣና እኔ ስገባ የተጠቀመበትን ፎጣ ዐየሁት፡፡
ታጥቦ ያልተጨመቀ ብርድልብስ ያህል ረጥቦ፣ ማንጠልጠያው ላይ በሰላም ተሰቅሎ የነበረው የእኔ ደረቅ ሮዝ ፎጣ ላይ ተደርቦ ተሰጥቶ ጠብ… ጠብ… ይላል፡፡
ይሄ ነገር በማይገባኝ ምክንያት ከዚህ በፊት የማውቃቸው ወንዶች ሁሉ፣ ኧረ እንዲያውም ሁሉም ፎጣ የሚጠቀም ወንድ፣ የትም የሚያደርገው ነገር ነው፡፡ በጣም የሚቀፈኝ ነገር፡፡ እርጥብ ፎጣ፡፡ ጠብ ጠቡ፡፡ ሽታው፡፡
በዚያ ላይ ደረቅ ፎጣዬ ላይ ተደርቦ….
ዛሬ ግን ግድ አልሰጠኝም፡፡
የዚያን ዕለት አብረን አድረን ጠዋት ሻወር ሲገባ አድርጌ የማላውቀውን፤ ለማንም የማልሰጠውን ሽቶ የተቀባ ደረቅ ፎጣዬን እንካ አልኩት፡፡
ነግቶ ቁርስ ስንበላ፣ ፊልም ላይ እንዳሉ ወንዶች ሳይንበረከክ፣ እንደ ዘመኑ አርቲስቶች ሳይቅለበለብና ወሬ ሳያበዛ፣ ቅልብጭ ያለች ሚጢጢ ነጭ ፈርጥ ያላት ቀጭን የወርቅ ቀለበት፣ ከአንዲት ቀይ ጽጌረዳ አበባ ጋር አውጥቶ ሰጥቶ እንዳገባው ጠየቀኝ፡፡
ቀለበቷ፣ አይነግቡ ባትሆንም፣ ለወራት ሳያሳልስ ቆጥቦ እንደገዛት ዐውቃለሁ፡፡ ያ የበለጠ እንድወዳት አደረገኝ::
---
ከስድስት ዓመታት ትዳርና ሁለት ለማየት የሚያሳሱና እሱን የሚመስሉ ሴት ልጆችን ካፈራን በኋላ፣ ቀጭኗ ቀለበት ጠባኝ ብትቀመጥም፣ ያቺ አበባ- ከጊዜ ብዛት ከቀይ አበባነት ይልቅ ለቡኒ ዱቄትነት ብትቀርብም- አሁንም በክብር ያስቀመጥኳት ክፍት ሳጥን ውስጥ አለች፡፡
ይሄ ሰው ቢያረፍድም እንኳንም መጣ፡፡