ትራማዶል የተሰኘ ክኒን፣ ሲጋራና ጥሬ ገንዘብ ለሕግ ታራሚዎች ለማስገባት የሞከሩ ግለሰቦች በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ
*********
በዝዋይ ማረሚያ ማዕከል የሕግ ታሚዎችን የሚያስተምር መምህር እና ከአዲስ አበባ ታራሚ ጥየቃ የሄደ ግለሰብ ወደ ማረሚያ ቤት እንዳይገቡ የተከለከሉ ነገሮችን ለማስገባት ሲሞክሩ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳያቸው በባቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሲጣራ ቆይቷል።
የሁለቱንም ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የያዘው የአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት የባቱ ከተማ ኗሪ እና የ1ኛ ደረጃ መምህር የሆነው አቶ ሁሴን ጊሌ ሚያዚያ 9/2017 ዓ.ም 200 ፍሬ ትራማዶል እና 7 ሺህ ብር ደብቆ ለሕግ ታራሚዎች ሊያስገባ ሲል ስለመያዙ የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ ሚያዚያ 16/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ6 ወር እስራት እና የ2 ሺህ ብር ቅጣት ወስኖበታል።
በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ታራሚ ለመጠየቅ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ማዕከል የሄደው ወጣት ፍሬዘር ብርሃኑ መጋቢት 25/2017 ዓ.ም በያዘው የምግብ ሳህን ውስጥ ሌላ ሳህን ደርቦ ትራማዶልና ሲጋራ ለማስግባት ሲሞክር በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ተይዞ በባቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ ሲጣራበት ቆይቷል።
ምርመራው ተጠናቅቆ የቀረበለት የአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ተከሳሹ ጥፋኛ መሆኑን አረጋግጦ ግለሰቡን ያስተምረዋል ያለውን የ6 ወር እስራት እና የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደወሰነበት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።