ቡና ርኩስ ነውን?
አንድ አንድ ሰዋች "ቡና ርኩስ ነውና አይጠጣም" ለማለት የሚያቀርቡትን ምክንያቱች ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸው ከእውነት የራቁ መሆኑን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
በመጸሐፍ ተከልክሏል የሚሉ አሉ
አንድ አንድ ሰዋች በድርሳነ ጽዩንና በዜና ሥላሴ ተከልክሏል ይላሉ፡፡እስካሁን ግን ምዕራፍና ቁጥር ወይም አንቀጽና ገጽ ጠቅሶ ይህን የሚል የለም ፡፡በርግጥ መጻሕፍቱ ለምዕመኑ በቅርብ ባለመገኝታቸው ለማሳመኛ ተጠቅመውባቸው ካልሆነ በስተቀር፡፡በሁለቱም መጻሕፍት ቡና አትጠጡ የሚል ነገር እንደሌለ ያነጋገርናቸው ሊቃውንት ገልጠውልናል፡፡
የዲያብሎስ መሥዋዕት(ደም) ነው የሚሉ አሉ
ለዲያቢሎስ የተፈጠረ ወይም የተለየ መሥዋዕት እህል ተክል ወይም እንስሳ የለም አንድ አንድ ሰዋች ያልተማሩትን ከመጻሕፍም ከሊቃውንትም ያላገኙትን እየተረጎሙ "ቡናው የዲያብሎስ ደም የቡና ቁርሱ የዲያብሎስ ሥጋ ነው)በማለት ከሥጋ ወደሙ ጋር አመሳስለው ለመተርጎምና ለዲያቢሎስ ለመስጠት ያስባሉ ትልቁ ኃጢአትስ የእግዚአብሔርን ፍጥረት የዲያብሎስ ነው ብሎ መስጠት ነው፡፡
አንድ ሰው ለዲያቢሎስ ነው ምሠዋው ብሎ እስካመነ ድረስ<ቡናም ሻይም በግም ዶሮም ቆሎም ቢሠዋ እንደ እምነቱ ለዲያቢሎስ ባርነቱን ይገልጻል፡፡በመሆኑም ይህ ትምህርት ከእውነት የራቀ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት የሌለው ነው፡፡
የተወገዘ ነው የሚሉ አሉ
አንድ አንዶች ቡና በቤተክርስቲያን የተወገዘ ነው ብለው ያምናሉ ይናገራሉ ያወገዘው ማን እንደሆነ ግን አይገልጡም ለመሆኑ የማውገዝ ሥልጣን ያለው ማን ነው ?ውግዘቱስ የሚጸናው መቼ ነው አንድ አንዶች ባሕታዊ እገሌ አውግዘዋል የሚሉት ፈሊጥ አላቸው አንድ ውግዘት የሚጸናውየሚያወግዘው ትክክለኛ የክህነት ሥልጣን ካለው፡፡ያወገዘበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን በደነገገችው መሠረት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ከዚህ ውጪ የሚደረግ ውግዘት ግን "ግዝት ዘበከንቱ" ተብሎ ይጠራል፡፡
አንድ አንድ ጊዜ ለአንድ አካባቢ ወይም ለአንድ ዘመን ተብሎ የወጣ ሕግና ሥርአት ሳይታሰብ ሁሉንም ቦታ የሚያዳርስበት ጊዜ አለ ፡፡በአንድ አንድ አድባራትና ገዳማት ቀዳስያኑ መነኮሳት ብቻ እንዲሆኑ ሥርዓት ዓለ ይህ ማለት በሌሎቹ ም አድባራት ሕጋውያን ካህናት መቀደስ የለባቸውም ማለት አይደለም በአንድ አንድ ገዳማት ከበሮ እንዳ ይመታ ይከለከላል ይህ ማለት ግን ከበሮ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ቡና መጠጣትም በአንድ አንድ ቅዱሳት ገዳማት ተከልክሎ ይሆናል ይህ ግን ተናጥላዊ ሥርአት ብቻ እንጂ የቤተክርስቲያን ሁሉ ዐቀፍ ሥርዓት ነው ማለት አይደለም፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን የቡናን ርኩስነት በመግለጽ በቤተክርስቲያን አበው የተላለፈ ውግዘት የለም፡፡
ክርስቶስ ሲሰቀል ለምልሟል የሚሉ አሉ
ቡናን በተመለከት የሚነሣው አስገራሚ ታሪክ ጌታችን ሲሰቀል ቡና ጫት ትምባሆ ለምልመዋል እየተባል የሚነገረው ነው ጌታችን ሲሰቀል ሦስት <<ዓመጸኛ>> ዛፎች አልደረቁም ማለታቸው በቤተክርስቲያን ታሪክ ያለተመዘገበ አፈ ታሪክ ነው አእምሮ ልቡና ኖሯቸው እንደ ይሁዳ ዓመጹ እንዳይባል እንጨቶች ናቸው ታዲያ ምን ሆነው ለምልመው ተገኙ
ከዚህም በላይ ጌታችን ሲሰቀል የተፈጸሙት ሰባት ተአምራት ምን ምን እንደሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት በዝርዝር ተቀምጠዋል ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፣ ከዋክብት ረገፉ፣ መቃብራት ተከፈቱ፣ ዓለቱች ተሰነጣጠቁ፣ ሙታነ ተነሡ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከታች ከሁለት ተቀደደ ከዚህ ውጭ ሦስት ዛፎች ሳይደርቁ ቀሩ የሚል ትምህርት ግን የለም፡፡
በአርዩስ ፈርስ ላይ የበቀለ ነው የሚሉ አሉ
አርዮስ በክሕደቱ ጸንቱ ሆዱ ተዘርግፎ ሲሞት በፈርሱ ላይ አስቀድመው የተጠቀሱት ሦስቱ ዕጽዋት በቅለዋል ይባላል ይህ ከላሜ ቦራ ተረት ያልተናነሰ ነው የኒቂያን ጉባኤ ታሪክ የአርዮስን አሟሟት የጻፉ የውጭ ሀገርም ሆነ የሀገር ውስጥ የታሪክ ሊቃውንት ይህን ጉዳይ መቼም ቢሆን ጽፈውት አንስተውት አያውቁም፡፡
ነገር ግን ውሸት ሲቆይ እውነት ይመስላል እንደሚባለው የሆነ እንጂ ይህን ትምህርት የሚያስፋፉትም ቢሆን ከቤተክርስቲያን የታሪክ መጻሕፍት ልብ የሚሞላ መረጃ አያቀርቡም፡፡
በሌላም በኩል ዕጽዋት ተፈጥረው ያለቁት በዕለተ ሠሉስ መሆኑን ኦሪት ዘፍጥረት ይገልጥልናል ፍጥረት መፍጠርም በዕለተ ዓርብ ተጠናቋል ታዲያ በአርዩስ ፈርስ ላይ እነዚህ ፍጥረታት ከበቀሉ አዲስ ፍጥረት ሆነው ከብዙ ሺህ ዘመናት በኀላ ተገኙ ልንል ነው ይህ አባባል ከሥነ ፍጥረት ትምህርት ጋር የሚቃረን የስሕተት ትምህርት ነው፡፡
ባዕድ አምልኩ ነው የሚሉ አሉ
ማንኛውም ነገር ባዕድ አምልኮ የሚሆነው ለእግዚአብሄር ሊፈጸም የሚገባው ነገር ለዚያ ነገር ሲደረግለት ነው፡፡በእርግጥ አንድ አንድ ሰዋች ከትምህርት ማነስ ቆሎ የመሚበትኑ ስኒ እያዩ የሚጠነቁሉ ቡና ካልተወቀጠና ካልተፈላ በቤቱ ክፉ ነገር እንደሚገጥም ወዘት የሚያስቡ አሉ ይህ ግን የሰዋቹ በእምነት ያለመብሰልና ስለ ቡና ያላቸው የተዛባ አመለካከት የፈጠረው ነው እንጂ ቡና አምልኮ በዓድ በመሆኑ የመጣ አይደለም፡፡
ለምሳሌ ቂጣ ቆርሰው ቅቤ ቀብተው የሚበሉ አሉ ይህ ግን ቂጣ በቂጣነቱ አምልኮ በዓድ አያደርገውም፡፡ዶሮ አርደው የሚጥሉም አሉ ይህም ቢሆን ዶሮን በዶሮነቱ አምልኮ በዓድ አያደርገውም ፡፡ማንኛውም ነገር በሚገባ ካልተጠቀሙበት መልኩን የማይቀየርበት ምክንያት የለም፡፡
በጠቅላላው
አንድ ዛፍ በተፈጥሮ መልካም ሆኑ ሳለ ሰው ግን ዛፉን ቆርጦ ጠርቦ ጣዖት አድርጎ በሚሠራው ጊዜ ርኩስ ይባላል ርኩስ ያሰኘው የተጠቃሚው ሰው እኩይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡እንጨቱ በጥንት ተፈጥሮ ርኩስ እንዳልነበር የታወቀ ነው፡፡እንደዚሁ ሁሉ ቡናም ፍሬው በጥንት ተፈጥሮው ጥሩ ሆኖ ሳለ ተጠቃሚው የሰው ልጅ ግን ለርኩስ መንፈስ መሥዋዕት አድርጉ ሲያቀረበው ሲያቀርበው ርኩስ ይሆናል፡፡ለባዕድ አምልኮ ተብሎ ከተፈላ ጠጭውንም ያረክሰዋል፡፡
ቡና መጠጣት አለበት ከተባለ በቡናነቱ ብቻ መጠጣት አለበት የአድባር የቆሌ መለመኛ ከሆነ ግን አጠቃቀማችን ቡናን ለአምልኮ በዓድ አድርጉታልና ቡናውን ከዚህ መለየት ካልቻልን አብረን ልንተወው የተገባ ነው፡፡
በሌላም በኩል ቡና የሐሜተኞች መሰባሰቢያ ሆኖ የሚያገለግልበት ጊዜ አለ እዚህ ላይ ሀሜቱን ያመጣው ቡናው ሳይሆን ሰዋች በቡና አማካኝነት መሰባሰባቸውን ርዕስ ወሪያቸው <ነገረ ሰብእ> መሆኑ ነው፡፡
በእርግጥ የቡና ሱሰኛ ሆነው ያለ እርሱ የማይሠሩ የማይነቁና የማያስቡ ካደረጋቸው መተዋቸው ተገቢ ነው፡፡
በጠቅላላው ቡና መጠጣት የለበትም የሚለው ትምህርት ግን የቤተክርስቲያን ትምህርት አይደለም በእርግጥ ከቡና ጋር ተያይዘው የሚመጡትን አጉል ልማዱችና አምልኮዋችን ያላቸውን ጉዳዩች ሕዝቡ እንዳይፈጽም ማስተማር ተገቢ ነው፡፡
ምንጭ፡- ቃለ ተዋሥኦ ፪
ለወዳጆ ያጋሩ 📲
👇🏼👇🏼👇🏻👇🏼👇🏻👇🏼
@menifesawimenigedi