‹‹ቀብር እና ማስካራ››
----------
ቀብሩ ላይ ብዙም አላለቀሰችም፡፡ ለቀስተኛው የሚጠብቅባትን ያህል አላለቀሰችም፡፡
በመሪር ሃዘን ጭብጥ ብላ አለማንባቷን ብዙ ሰዎች አስተውለውታል፡፡
አንደኛዋ አክስቷ ፣ “ምን ጉድ ነው!…የሩቅ ዘመድ የሞተባት እንኳን አትመስልም እኮ!›› ብላለች፡፡
የአጎቷ ልጅ ‹‹ ለነገሩ እሷ ከልጅነቷ ጀምሮ ልቧ ድንጋይ ነው፡፡ የሚገርማችሁ ህጻን ሆነን በግ ታርዶ ደሙ ሲንዠቀዠቅ እኛ እሪ ስንል እሷ ግን ፍጥጥ ብላ ታየው ነበር፡፡ ግን ቢያንስ ዛሬ እንዲህ ትሆናለች ብዬ አላሰብኩም ነበር›› ስትል ተሰምታለች፡፡
ቄሱ ለገላጋይ የሚያስቸግሩ ሃዘንተኞችን በአሳር በመከራ ማፅናናት ስለለመዱ በሁኔታዋ ግር ተሰኝተው አሁንም አሁንም ሰረቅ አድርገው ያይዋት ነበር፡፡
ሁሉም ሰው አጠገቡ ካለው ሰው ጋር የሚንሾካሾከው ስለ ሟችና አሟሟቱ ሳይሆን፣ ጎርፍ ሆኖ ስላልወረደው እምባዋ፣ በሀዘን ስላልጠወለገው ፊቷ ነው፡፡
አፈር ሊያለብሱት ሲቃረቡ ግን አዲስ በተቆፈረው ጉድጓድ አጠገብ ተንበርክካ ያለ እንባ አነባች፡፡ ሰው የሚጠብቀውን አይነት ሃዘን በዋይታና በጩኸት ልታሳይ ተጣጣረች፡፡
ከውስጧ ተገፍታ ሳይሆን ሰዉ ምን ይለኛል ብላ፡፡
ወፈ ሰማዩ ለቀስተኛ ያላወቀው ነገር ቢኖር እነሱ ዛሬ አልቅሰው ሊሰናበቱት የመጡትን ባሏን ከማንም ቀድማ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በዳሸን ባንክ ቢሮ ውስጥ ለብቻዋ፣ አልቅሳ መቅበሯን ነው፡፡
ብር ለማውጣት ሄዳ ያስተናገዳት ባለሙያ ከወራት በፊት የጋራ ቁጠባ ሂሳባቸው ውስጥ ያለውና ንብረት ሊገዛበት የተቀመጠው በጣም ብዙ ገንዘብ ሁሉ ሙልጭ ተደርጎ መውጣቱንና አካውንቱ መዘጋቱን ዝግ ብሎ ሲገልጽላት።
"ለምንድነው የጋራ ሂሳቡን ሲከፍቱ or ከማድረግ ይልቅ and ያላደረጉት?" አለ የደነገጠ ፊቷን እያየ።
ኦር…? ኤንድ?
‹‹የጋራ አካውንት ሲሆን እኔ ወይም እሱ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንችላለን ሳይሆን እኔ እና እሱ ቢሆን ይሻል ነበር…አብረን ካልመጣን አንዳችን ማውጣት አንችልም እንደማለት…›› ብሎ ሊያስረዳት ሞከረ፡፡
የሚላት ነገር አልገባትም።
እኔ እና እሱ እኮ ባልና ሚስት ነን፡፡
እኔ እና እሱ እኮ አንድ አካል አንድ አምሳል ነን፡፡ እኔ ማለት እሱ፣ እሱ ማለት እኔ ነን፡፡
እኔ መጣሁ እሱ ያው እኮ ነው ብላ ልትነግረው ሞከረች፡፡
በየዋህነቷ ይሆን የሚላትን ልትረዳው ባለመቻሏ አዘነላት፡፡
--
ሁሉ ነገር ተናውጦባት ከባንኩ ወጣች።
ወደ ቤቷ ሄደች፣ ከቤት ሰራተኛዋ ጋር ለልጆቸዋ መክሰስ አብስላ፣ እንባዋ ዝም ብሎ ሲፈስ ‹‹ሽንኩርቱ እኮ ነው›› ብላ ሰራተኛዋን ዋሸች፡፡
ልጆቿ ከትምህርት ቤት፣ እናቷ ለጉብኝት ሲመጡ አብራቸው በዝምታ ተመገበች፡፡
ምን ልትል ትችላለች?
ባሏ እድሜ ልክ የቆጠቡትን ገንዘብ ሁሉ ትልቅ ቂጥ እንጂ ሃፍረት ላልፈጠረባት የሃያ አራት አመት ገርልፍሬንዱ ማስተላለፉን ምን ብላ ትናገር?
----
ከዚያ በዝምታ ሁሉን ነገር ከስር ከመሰረቱ ማጣራት ጀመረች። ከጓደኞቿ ጋር።
ብዙ ሳትቆይ ከገርልፍሬንዱ ልጅ ስለመውለዱ አወቀች፡፡
ኢንስታግራም ላይ በተለጠፈ ፎቶ አማካኝነት፡፡ መጀመሪያ የቤቢ ሻወር ድግስ፣ ከዚያ ደግሞ የህጻኑን መወለድ በማስመልከት የተለጠፈ የኬክና የህጻኑ ፎቶዎችን አይታ፡፡
‹‹ዌልካም ቤቢ ኔታን›› ከሚለው ብረት ምጣድ የሚያህል ሰማያዊ ኬክ አጠገብ በጀርባው ተንጋሎ የሚታየው ህጻን ገና ካሁኑ ቁርጥ እሱን፡፡ የክህደቱ ማስረጃ፡፡
ስላደረገው ነገር እንደምታውቅ አሳውቃው አልጋፈጠችውም።
በጓደኞቿ ምክር መሰረት ረጋ ብላና አስባ ከሚገባት ንብረት ጋር ልጆቿ ጋር የምታመልጥበትን እቅድ በማውጣት ራሷን ከእሱና ከሕይወቱ በዝግታ መነጠል ጀመረች።
የጋራ ሕይወታቸውን ቀስ በቀስ የእሷ ብቻ የሚያደርጉ ቋንቋዎችን እያደር ለመደች፡፡
እንደ በፊቱ ‹‹እማዬ›› ከማለት “እናትህ እሁድ እመጣለሁ ብላለች›› ፣
እንደ ድሮው ‹‹ቤታችን ›› ሳይሆን "ይሄ ቤት"
እንደ ደህናው ጊዜ ‹‹ልጆቻችን› ሳይሆን ‹‹ልጆቼ›› እያለች በትንንሽ የአርትኦት ስራዎች፣ በጥቃቅን እርማቶች ከእሱ ጋር እየኖረች ካለ እሱ መኖርን መለማመድ ጀመረች፡፡
ሳትርቀው ተለየችው፡፡ ሳትፈታው ተፋታችው፡፡
---
ከፖሊስ ጣቢያ ተደውሎ ስለደረሰበት ድንገተኛና አሳዛኝ አደጋ ሲነገራት የባሏን ክፉ የሰማች ሚስት አትመስልም ነበር፡፡
----
በቀብሩ ማሳረጊያ ላይ በቤተዘመድና በልጆቿ ተከባ በተቀመጠችበት ልጅቷን አየቻት።
ሰውነቷ ላይ ልክክ ያለ ለለቅሶ የማይሆን በጣም የሚያምር ጥቁር ከፋይ ቀሚስ ለብሳ። የሚያንጸባርቁ ነጫጭ ፈርጦች ያሉት ቢጢሌ ጥቁር ሻርፕ እንደነገሩ ጣል አድርጋበት፡፡ በወሊድ ይባስ የወፈረ ቂጧ ተንጠልጥሎ፡፡ እንባዋ ያጠበው ማስካራዋ የትላልቅ አይኖቿ ድምበር ላይ ጥቁር ደለል ሰርቶ፡፡
ዓይኖቿን አሁንም አሁንም በሶፍት ስትጠራርግ አየቻት፡፡
ከዚያ ደግሞ ወደ ሰማይ አንጋጣ፡፡
ለሃጥያቷ ሥርየት እየጠየቀች ነው ወይስ በትንሹ በትንሹ የሚወርደው እምባዋ የቀረ ማስካራዋን ጠርጎ ይበልጥ እንዳያጨማልቃት ሰግታ..?
አላወቀችም፡፡
የልጅቱን ሁኔታ ስታይ ለአፍታ ባሏ ቀና ብሎ ቢያያት ምን እንደሚሰማው አሰበች፡፡
ያንን ሁሉ ደባ ሸርቦ የልጆቹን እናትና የልጆቹን ንብረት ያለማንገራገር ያስረከባት ቅምጡ ለቀብሩ ማስካራ ተለቅልቃ መምጣቷን ቢያይ ምን ይል ይሆን? ብላ፡፡
ድጋሚ ሰርቃ ስታያት አይኖቻቸው ተገጣጠሙ፡፡
ነፍስ ይማር እያለ ሊሰናበታት መጋፋት የጀመረውን ለቀስተኛ ማስተናገድ ከመጀመሯ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ አተኩራ አየቻት፡፡
ልጅቱም አጸፋውን መለሰች፡፡
በዚያች ቅጽበት በሁለቱ ሴቶች መሃከል ከእነሱ ውጪ ማንም ሊረዳው የማይችል የአይን ብቻ ንግግር ነበረ፡፡
የባሏ ቀብር ላይ እምብዛም አላለቀሰችም፡፡