አባቴ ጥቁር ነበር ፊቱ አይፈታም። ወታደር ነበር መቶ አለቃም ነበር ። ፀጉር ጥቅጥቅ ያለ ነበር ። አናፂ ነበር ። ብዙ አያወራም ነበር ።
ይወደኝ ነበር ። ያለውን ብር አውጥቶ ሱሪ ጥልፍልፍ ጫማ አቡወለድ ይገዛልኛል ። አታጨማልቀው ይሉት ነበር ። መቶኝ አያውቅም ።
ከጁ ሲጋራ ከእጁ እኔ አልጠፋም ነበር ። ሲጋራ ሽታው አባቴን ስለሚያስታውሰኝ ሲጋራ እወዳለሁ ። ሲጋራ አጤሳለሁ ።
አባቴ ኮስተር እንዳለ ነበር ውለታ የሚውለው ። አኮሰታተሩ አዲስ ሰው አያቀርብም ። የቀረበው ሁሉ ግን ይወደዋል ። ዝናብ ይወድ ነበር ። ፀሃይ ከረረ ብሎ አይነጫነጭም ብርድ ነው ሙቀት ነው እያለ ስለ አየር ሁኔታው አያብራራም ። ከተፈጥሮ ጋ ሲጨቃጨቅ ሰምቼው አላቅም ።
አባቴን እወደዋለሁ ። አይኑ ላይ የማየው ቸርነት እና ፍቅር የትም ስፍራ የትም ፊት ላይ አይቼው አላውቅም ። ምንም ነገር ለኔ ከሆነ ሲሳሳ አይቼ አላውቅም ። አለም ላይ ብቸኛ እንድበልጠው የሚፈልገው አባቴ ነው ።
አባቴ ሲናፍቀኝ ፎቶውን አያለሁ ኮቱን እለብሳለሁ ። ያለኝን አስታውሳለሁ ። ሳላማርር እናፍቀዋለሁ ። ከተፈጥሮ ጋር ሳልጨቃጨቅ ያወረሰኝን መልካምነት እኖረዋለሁ ።
።
መልኬን እምወደው ስለማምር አይደለም እሱን ስለምመስል ነው። አምሳያዬ ሶስት ቀን ብሎኝ ያውቃል ። እሱ እወዳቸዋለሁ ያለኝን ሰዎች ሁሉ እወዳቸዋለሁ ።
ናፈቀኝ .....ማግኘት የሌለበት ናፍቆት ደስ አይልም መሰለኝ ።
© Adhanom Mitiku